የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የመግፋት ሙከራ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ይጻረራል

By Hailemaryam Tegegn

May 08, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የመግፋትና በር የመዝጋት ሙከራዎች ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጻረሩ መሆናቸው ተመላከተ፡፡

በተለይም አንዳንድ ሀገራት በቀይ ባሕር ጉዳይ እያራመዱት ያለው በር የመዝጋት አካሄድ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ሕግ ባለሙያ አበበ ከበደ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ግብጽ ሰሞኑን የቀይ ባሕርን ጉዳይ የተጎራባች ሀገራት ብቸኛ ኃላፊነት በማስመሰል እያሰራጨች ያለው ጉዳይ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ተራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አንድ ዕድል ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የዓለም አቀፉ የባሕር ሕግ መርሆዎች የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የሚደግፉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ሕግ መሠረት በማድረግ ለቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነት ያቀረበችውን የባሕር በር ጥያቄ የመግፋትና በር የመዝጋት ሙከራዎች ተቀባይነት እንደሌላቸውም ነው ያስረዱት፡፡

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለመጠናቀቅ ከጫፍ መድረሱ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሳድግና ቀጣናዊ ተጽዕኖና ተደማጭነቷን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትና የባሕር በር ጥያቄዋ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ማግኘቱ እንቅልፍ የነሳቸው ኃይሎች፤ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመለያየት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ በተለይም ከኬንያ እና ጅቡቲ ጋር ያላት የኢኮኖሚ፣ የንግድ እንዲሁም የሰላምና ደኅንነት ትብብር ጠንካራ መሠረት ያለው በመሆኑ ከቀጣናው ሀገራት የመነጠል ፍላጎቶች ሊሳኩ እንደማይችሉ አስታውቀዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በባሕር በርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ በተለይም የውኃ ዲፕሎማሲን በተመለከተ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ