የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ ይካሄዳል

By Yonas Getnet

May 08, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ ግንቦት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት፤ ጉባኤው ከጂ20 ኢንተር ፌዝ ፎረም፣ ከአፍሪካ ህብረትና በአፍሪካ ህብረት ስር ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።

የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሪዎችና ሌሎችም ይሳተፉበታል።

እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከ80 በላይ የሚሆኑ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የባህል መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ምሁራን ይሳተፋሉ ብለዋል።

ጉባዔው በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና በቀጣይ መስከረም በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

ጉባኤው በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በትምህርትና ሌሎች የልማት አጀንዳዎች ዙሪያ በመምከር ለቡድን 20 አባል ሀገራት ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የሃይማኖት መከባበርና የአብሮነት ልምድ ይቀስማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችና ታሪካዊ ቦታዎችን እንደሚጎበኙ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላምና መከባበር እሴት ግንባታ ላይ ከሚያከናውነው ተግባር በተጨማሪ ኢትዮጵያ የአፍሪካን አጀንዳ በማስተጋባት ያላትን ሚና እንድትቀጥል የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።