አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በእንጅባራ ከተማ እየተወያዩ ነው።
ውይይቱ በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን፤ በመድረኩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ለሰላም ወደ ሰላም በሯ ከተማ በሰላም መጥተናል በማለት በመድረኩ የገለጹት አቶ አረጋ ከበደ፤ የአዊ ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር አስማምቶ፣ ተፈጥሮን ተንከባክቦ ራሱን በሚመቸው መንገድ የሚመራ ሕዝብ ነው ብለዋል።
የአዊ ሕዝብ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ድር እና ማግ ሆኖ የሚኖር መሆኑን በመጥቀስ፤ የአዊ ሕዝብ ለሀገር እና ለአካባቢ ሰላም መሆን ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ሕዝብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕትነት የከፈለ እና የቀደሙ አባቶችን ገድል የደገመ ትልቅ እንደሆነ በማስታወስ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የሀገርን ሉዓላዊነት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግርም በሰከነ መንገድ ሰላሙን የጠበቀ አስታዋይ ሕዝብ እንደሆነ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ጽንፈኞች ሊፈጥሩት የነበረውን ያልተገባ ጉዳይ በጥበብ ያከሸፈ፣ አንድነቱን እና ሰላሙን የጠበቀ፤ ችግር እንኳን ቢኖር በሰላም መፈታት አለበት ብሎ የሚያምን አስታዋይ ሕዝብ ነው ብለዋል።
ትምህርት ከድህነት መውጫ፣ የእድገት ማረጋገጫ ነው ብሎ የሚያምን፣ ልጆቹን በልዩ ትኩረት የሚያስተምር ታላላቅ ምሁራንን ያፈራ አካባቢ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የአዊ ሕዝብ ባሕሉን እና ወጉን ጠብቆ ለትውልድ ያስተላለፈ እንደሆነ ገልጸው፤ ሕግ አክባሪ፣ ሰላም ወዳድ፣ በፍትሕ እና በዳኝነት የሚያምን፣ ችግሮችን በሽምግልና ሥርዓት የሚፈታ፣ የኃይል አማራጭን የማያስቀድም ብልህ ሕዝብ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ቀናዒነት፣ አስታዋይነት እና አርቆ አሳቢነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።