ስፓርት

ሞሐመድ ሳለህ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኗል

By abel neway

May 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብጻዊው የሊቨርፑል ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህ በእግር ኳስ ፀሐፊዎች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፏል፡፡

ሳላህ በውድድር ዓመቱ 28 ግቦችን በማስቆጠርና 18 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ሊቨርፑል የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል፡፡

በተጨማሪም በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ የጎል ተሳትፎ ክብረ ወሰንን ማሻሻል ችሏል፡፡

ሊቨርፑል በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ 16ቱን እንዲቀላቀል 3 ጎሎችን በማስቆጠር እና 4 የግብ ኳሶችን በማቀበል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ሳላህ የእግር ኳስ ማኅበሩን አባላት አብላጫ ድምጽ (90 ከመቶ) በማግኘት ያሸነፈ ሲሆን፤ ይህም በክፍለ ዘመኑ ከፍተኛው ድምጽ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የ32 ዓመቱ ተጫዋች ሽልማቱን ሦስት ጊዜ በማሸነፍም የፈረንሳዊውን ቴሪ ሄነሪ ሪከርድ ተጋርቷል፡፡

በዚሁ የምርጫ ሂደት ውስጥ የቡድን አጋሩ ቨርጂል ቫንዳይክ 2ኛ፣ የኒውካስል ዩናይትድ አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳቅ 3ኛ እንዲሁም እንግሊዛዊው የአርሰናል አማካኝ ዴክላን ራይስ 4ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

በተመሳሳይ በሴቶች እንግሊዛዊቷ የአርሰናል አጥቂ አሌሲያ ሩሶ በእግር ኳስ ማኅበሩ ፀሐፊያን የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋችነት ክብር ተጎናጽፋለች፡፡

የ26 ዓመቷ ሩሶ በፕሪሚየር ሊጉ ለአርሰናል ሴቶች ቡድን 12 ግቦችን አስቆጥራለች፡፡ እንዲሁም በሴቶች የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ 8 ግቦችን በማስቆጠር እና 2 የግብ ኳሶችን በማቀበል ቡድኗ ከባርሴሎና ጋር የፍጻሜ ተፋላሚ እንዲሆን አስችላለች፡፡

በአቤል ንዋይ