አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ስርዓት አልበኝነትን መዋጋቷን ትቀጥላለች ሲሉ ገለፁ፡፡
ሩሲያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ኃይል ወረራን በመመከት ያሸነፈችበት 80ኛ ዓመት የድል በዓል በመዲናዋ ሞስኮ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል፡፡
የድል በዓሉ በሞስኮ አደባባዮች በተለያዩ ወታደራዊ ስነ ስርዓቶች እንዲሁም የጦርነቱ ሰማዕታትን በማሰብ እየተከበረ ሲሆን በበዓሉ ልዩ ዝግጅት የኦርሺኒክ እና አር ኤስ 28 አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች እና ሌሎች ዘመናዊ ትጥቆች ለእይታ ቀርበዋል፡፡
በተጨማሪም የሩሲያ ኤር ስፔስ፣ ታንክ፣ ዘመናዊ ተሸከርካሪዎች እና ሌሎች ወታደራዊ ክፍሎች ትርዒት አቅርበዋል፡፡
በሞስኮ ሬድ ስኩዌር በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ፕሬዚዳንት ፑቲን ባደረጉት ንግግር÷ ሀገራቸው ሩሲያ ጠልነትን መዋጋቷን ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሀያላኑ የበርካታ ሀገራትን ግዛት በማለፍ በደሎችን ሲፈጽሙ እንደነበር አስታወሰው፣ ይህንን በደል በወቅቱ የነበረው የሶቭየት ሀይል መቀልበስ መቻሉን ተናግረዋል።
ድሉ ሩሲያ ያላትን ሀቅ ለዓለም ያሳየችበት እንደበር ገልፀው፤ ሊጨቁኑ የመጡትን ኃይሎች በመፋለም አባት ሀገር ላስረከቡን ጀግኖቹ የሶቭየት ወታደሮች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ሩሲያ እውነት ስለነበራት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ኃይልን አሸንፋለች በማለት ገልጸው÷ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ትምህርት መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሩሲያ የድል ቀን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የ20 ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ