አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲፋጠን ዳያስፖራው የጎላ ሚና አለው ሲሉ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሁሉም አካባቢዎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት የኢትዮጵያውያን ሳምንት በአቡዳቢ እየተከበረ ይገኛል።
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የንግድ ማህበረሰብ አባላት እና በሀገር ቤት የሚገኙ የቢዝነስ ድርጅቶችን ለማስተሳሰር ያለመ የቢዝነስ ፎረም ተካሂዷል።
የኢትዮጵያውያን ሳምንት ፌስቲቫል አካል የሆነው የቢዝነስ ፎረምን የከፈቱት አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ/ር)፤ የሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲፋጠን የዳያስፖራው ሚና የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ በማድረግ ሂደትም ዳያስፖራው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተመሳሳይ የቢዝነስ ፎረሞችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአቡዳቢ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በከተማዋ ያዘጋጁት የጋራ የቢዝነስ ፎረም ሲካሄድ፤ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ከአቡዳቢ የንግድ ቻምበር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
በሳምራዊት ተወልደ