የሀገር ውስጥ ዜና

የአርባ ምንጭ ስታዲየም ለስፖርት ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ አለው – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

By Abiy Getahun

May 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) መስፈርት መሰረት እየተገነባ ያለው የአርባ ምንጭ ስታዲየም ለሀገሪቱ የስፖርት ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የፌደራልና የክልል አመራሮች የአርባ ምንጭ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ ያለበትን ደረጃ እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን በተመለከቱበት ወቅት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት፤ የአርባ ምንጭ ስታዲየም ለሀገሪቱ የስፖርት ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል።

በተለይም በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ ዘርፎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።

አርባ ምንጭ እና አካባቢው የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚፈልቁበትና የስፖርት ቤተሰብ በብዛት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ስታዲየሙ በአካባቢው መገንባቱ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በህዝብና በመንግስት ትብብር እየተገነባ ያለው የስታዲየም ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

አፈ ጉባኤው በሀገር ደረጃ እየተገነቡ ያሉ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድና ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ብልጽግና በተጨባጭ እያረጋገጡ እንደሆነ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው ህዝብ ለግንባታው መጠናቀቅ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የስታዲየሙ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለኢኮኖሚ እና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።