ፋና ስብስብ

የዓመት ፍጆታን እንደዋዛ በአንድ ቀን…

By ዮሐንስ ደርበው

May 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንደየአካባቢያቸው ባህል እና የአኗኗር ዘዴ ላይ ተመሥርተው ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ይጠቀማሉ፡፡

ለምሳሌ፤ ግጭት የሚፈታበት ስልት፣ የአንዱን ችግር የጋራ በማድረግ የመረዳዳት ልማድ፣ መድኃኒትን የመቀመም ዕውቀት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

በእነዚህ ዕውቀቶች እየታገዙም አንዱ ለሌላው በማሰብ፣ ኑሯቸውን በማቅለል እና ህመማቸውን በማከም ይኖራሉ፡፡

ከላይ ከተገለጹት ብሔረሰቦች መካከል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት የየም ብሔረሰብ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ብሔረሰብ በርካታ በሽታዎችን የሚፈውስ ነባር የሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤት ነው፡፡

በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ተመስርተው መድኃኒት የሚቀምሙ ሰዎች በብሔረሰቡ ውስጥ በስፋት ይገኛሉ።

በባህላዊ የሕክምና ዘዴያቸውም በአካባቢው የሚገኙ ዕፅዋትን በተካኑት ልምድ መሠረት ይቀምማሉ፡፡

ለዚህ ቅመማ የሚያስፈልጋቸውን የመድኃኒት ግብዓት እና ዓይነት ደግሞ በየጊዜው ፍለጋ አይወጡም፡፡

በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን ለዓመት የሚሆን ፍጆታቸውን በአንድ ዕለት የብሔረሰቡ አባላት በርከት ብለው በነቂስ በመውጣት እጽዋቱ ወደ ሚገኙበት የቦር ተራራ በመትመም ይለቅማሉ እንጂ፡፡

ይህ ባህላዊ መድኃኒት የሚለቀምበት እና ከባሕር ወለል በላይ 2 ሺህ 939 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የቦር ተራራ፤ ከአዲስ አበባ 271 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከየም ዞን አሥተዳደር መቀመጫ ሳጃ ከተማ በ32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በየም ዞን ከሚገኙት ተራሮች ትልቁ እንደሆነ የሚነገርለት የቦር ተራራ አናት ላይ ሲወጣ፤ በአራቱም አቅጣጫ በርካታ ስፍራዎችን መመልከት ያስችላል፡፡

በየም ብሔረሰብ አባላት ዘንድ “የፈውስ ተራራ” ተብሎ የሚቆላመጠው የቦር ተራራ፤ የብዝኀ ሕይዎት ሀብቱን እየጠበቁ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙበት ነው።

በዮሐንስ ደርበው