የሀገር ውስጥ ዜና

በምሥራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ዘርፍ የልኅቀት ማዕከል ለመሆን እየተጋ ያለው ኮሌጅ

By Yonas Getnet

May 12, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጀኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በስልጠናው ዘርፍ የምሥራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ዘርፍ የልኅቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡

ተቋሙ የፀሐይ ኃይልን መነሻ አድርጎ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን የኮሌጁ ምክትል ዲን ሰባውዲን ሁሴን ተናግረዋል፡፡

እንደስልጠና በምሥራቅ አፍሪካ የልኅቀት ማዕከል የምንሆነውም በዚሁ የታዳሽ ኃይል ዘርፍ በምናከናውናቸው ሥራዎች ነው ብለዋል፡፡

የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ኃይል ማግኘት የሚቻልበት ስማርት ፖል በኮሌጁ መሠራቱን ጠቅሰው፤ ሰልጣኞችም የዚሁ ሙያ ባለቤት ሆነው እንዲወጡ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኮሌጁ አሰልጣኝ የሆኑት ዓለምሰገድ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ተቋሙ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ እንዲታወቅ የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኮሌጁ አካባቢ የሚገኙ መብራቶችን በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ መብራቶች ለመቀየር ሥራዎች መጠናቀቃቸውን እና ለናሙናም የተሠሩ መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡

በኢነርጂ ላይ የሚሠራ ሥራ በሰው ሃብት አስተዳደር ትርጉም ያለው ለውጥ ያሳርፋል ያሉት ደግሞ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ አማካሪ አዝመራ ከበደ ናቸው።

በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በመፍጠር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን መተካት እና ወደ ውጪ በመላክ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መገንባት እንችላለን ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት