አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የጅኦ ቱሪዝም እና ጂኦ ፓርክ ሃብቶችን በይበልጥ ለማልማት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ አስታወቁ፡፡
ዛሬ የተካሄደውን የጅኦ ቱሪዝም እና ጂኦ ፓርክ ወርክሾፕ አስመልክተው ሚኒስትሯ ለፋና ዲጅታል እንዳሉት፤ መድረኩ በኢትዮጵያ እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለውን የጅኦ ቱሪዝም እና ጂኦ ፓርክ ግንዛቤ የሚያጠናክር ነው፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጂኦ ፓርኮቻቸውን ካስመዘገቡ 50 ሀገራት በአፍሪካ የሚገኙት ሁለት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም በአህጉሪቱ የጅኦ ቱሪዝም እና ጂኦ ፓርክ ሃብት በሚገባው ልክ አለመልማቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
ከሁለቱ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ 12 የሚዳሰሱ፣ 6 የማይዳሰሱና 5 ጥብቅ ሥፍራዎች ማስመዝገቧን ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ጂኦ ቱሪዝም እና ጂኦ ፓርኮች ወደ ሀብትነት ያለመቀየራቸው ዋና ምክንያት በዘርፉ ያለው የግንዛቤ እጥረት፣ ቅንጅት እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች በሚፈለገው ልክ ባለመሠራታቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱና አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ መደረጉ፤ የጂኦ ቱሪዝምን ለማጥናት፣ ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ እንደሚፀድቅ ጠቁመው፤ ፖሊሲው የጂኦ ቱሪዝም ሀብቶችን ለመጠበቅ፣ የጂኦ ፓርኮችን ለመመስረትና ግንዛቤ በመፍጠር ሥራዎቸን ለማሳለጥ ከፍተኛ አቅም አንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ