የሀገር ውስጥ ዜና

ለሐጅና ዑምራ ተጓዦች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ – አየር መንገዱ

By Abiy Getahun

May 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለዘንድሮ የሐጅና ዑምራ ተጓዦች ቀልጣፋና ምቹ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ዘንድሮ ለ1 ሺህ 446ኛ ጊዜ የሚደረገውን የሐጅና ዑምራ ጉዞ አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚሁ ወቅት፥ አየር መንገዱ በየዓመቱ ለሐጅና ዑምራ ሃይማኖታዊ ጉዞ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዘንድሮ ጉዞ ስኬታማነት አየር መንገዱ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ላሳየው ቀጣይነት ያለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሀላፊ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፥ አየር መንገዱ ከኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሚጓዘው ህዝበ ሙስሊም በርካታ በረራዎችንና ሰራተኞችን በመመደብ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለሐጅ ተጓዦች ቀልጣፋና የላቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

የጉዞው ስርዓት እስኪጠናቀቅ ድረስም አየር መንገዱ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የዘንድሮ የሐጅና ዑምራ ጉዞ ከነገ ረፋድ ጀምሮ ወደ ስፍራው የሚደረግ ይሆናል።