የሀገር ውስጥ ዜና

ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት ሚና እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

By ዮሐንስ ደርበው

May 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስገነዘቡ፡፡

3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የሃይማኖት መሪዎች ለሀገር የሰላም ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና የበለጠ ማጉላት እንደሚገባቸውም በአጽንኦት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እርስበርስ መረዳዳትና መደጋገፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመወጣትና ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑንም አስረድተው፤ ሚናቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።