አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የአርኪዮሎጂና የጂኦሎጂ ስፍራዎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ግሎባል ጂኦፓርክስ መዝገብ ቢካተቱ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ያሳድጋሉ ተባለ።
ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ዩኔስኮ በጋራ ያዘጋጁት ቀጣናዊ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ወርክሾፕ ተሳታፊዎች በኦሮሚያና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሚገኙ የአርኪዮሎጂ እና የጂኦሎጂ ስፍራዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በመስክ ምልከታው የጥያ ትክል ድንጋይ፣ መልካ ቁንጥሬ ባልጩት የአርኪዮሎጂ ስፍራ እና በደቡብ ሶዶ ኬላ ከተማ አቅራቢያ በጨንጭ ሲልካ ሳንድ የተፈጥሮ ሀብት መገኛ ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ የጂኦሎጂ ስፍራዎች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥያ ትክል ድንጋይ እንዲሁም የመልካ ቁንጥሬ ባልጩት የአርኪዮሎጂ ስፍራ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ ወቅት ስፍራዎቹ በዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክስ መዝገብ ውስጥ ቢካተቱ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የመስክ ምልከታው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ከሚኒስቴሩ፣ ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደር የመጡ የቱሪዝም ቢሮ ሃላፊዎች፣ ከዩኔስኮ እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ የመጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የመስክ ምልከታው በነገው ዕለትም በቡታጅራ አካባቢ ያሉ የጂኦሎጂካል ስፍራዎችን ይጎበኛሉ።
በነፃነት ፀጋይ