አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወደ ሥራ በማስገባት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከውጭ ይገባ የነበረ 10 ነጥብ 34 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ምርት ማስቀረት መቻሉን የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት አፈጻፀም ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ የብድርና የኃይል አቅርቦትን በማሻሻል፣ የግብዓትና የገበያ ትስስር በመፍጠር በኮቪድ፣ በሰላም እጦትና በሌሎች ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ስራ በማስጀመር በዘርፉ መነቃቃት መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም በአምራች ኢንዱስትሪው መሻሻሎች በመምጣታቸው የዘርፉ አማካይ የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 61 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በቱሪዝም ዘርፍ ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማደስና አዳዲስ መደረሻዎችን በመገንባት ተመራጭነትን ማሳደግ መቻሉንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
በተጨማሪም በኮንፈረንስ ቱሪዝም መስክ ባለፉት 10 ወራት ብቻ 84 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በተለያዩ ተቋማት አስተናጋጅነት መከናወናቸውን ገልጸው፥ በዘርፉ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም ከ30 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች እና ከ171 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን እንዲሁም ከጉባኤዎቹ ባሻገር ቆይታቸውን አራዝመው ሀገሪቱን እንዲጎበኙ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ወር ብቻ በቅርቡ የተካሄዱትን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ፣ የቀጣናዊ ደህንነት ፎረም እና የሃይማኖት ጉባዔን ጨምሮ ስምንት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ ተገልጿል።
በዘመን በየነ