አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለ2017/18 የምርት ዘመን እስካሁን 6 ነጥብ 16 ሚሊየን በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልል ገብቶ እየተሰራጨ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ታከለ ቁሩንዴ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷የአፈር ማዳበሪያን በተገቢው ሰዓት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በምርት ዘመኑ 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ጠቁመው ÷ አሁን ላይም 6 ነጥብ 16 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ እየተሰራጨ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ክልሉ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 1 ነጥብ 55 ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው አርሶ አደሩ እጅ መድረሱን አብራርተዋል፡፡
ቀሪውን ማዳበሪያ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከዩኒየኖችና እና ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በሥርጭት ሒደት ላይ ሊስተዋሉ የሚችሉ ሕገ ወጥ አሰራሮችን ለመከላከልም በተዋረድ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሕብረተሰቡ በአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ላይ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ