በአማራ ክልል የቀጠለው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሥራ

By Mikias Ayele

May 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የተጀመረው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ወ/ሮ ባንቺአምላክ ገብረማሪያም ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ለማጣራት የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።

የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ሥራው በሶስት ዙር እንደሚከናወን ጠቅሰው÷ በመጀመሪያው ዙር የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ማስረጃ ላይ ማጣራት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ለዚህም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች የትምህርት ማስረጃቸውን ለኮሚቴው ማስረከባቸውን ገልፀዋል፡፡

በሁለተኛ ዙር ደግሞ በክልል ደረጃ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም በሶስተኛው ዙር የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ ባለሙያዎች ማስረጃ ማጣራት እንደሚከናወን አመላክተዋል፡፡

በክልሉ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የመንግስት ሰራተኞች ቢኖሩም የማጣራት ሥራውን ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማስረጃ የማጣራት ሥራው ብቁ የሰው ሀይል ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ሐሰተኛ ማስረጃ በሚገኝባቸው አመራሮች እና ባለሙያዎች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከተው አካል የሚቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ አረጋ ከበደ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሥራ ሚያዚያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ ለዘላቂ ልማት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚተጋ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት የሰው ሀይል ግንባታ ማሻሻያው በቁርጠኝነት ይፈፀማል ማለታቸው ይታወሳል።

በሚኪያስ አየለ