ቴክ

በአህጉሪቱ ግዙፍ እንደሆነ የተነገረለት የድሮን ትርዒት በአዲስ አበባ ሰማይ

By Abiy Getahun

May 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 አካል የሆነው የድሮን ትርዒት ተካሂዷል።

በትርዒቱ 1 ሺህ 500 ድሮኖች ወደ ሰማይ የተለቀቁ ሲሆን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የደረሰችበት አቅም መንጸባረቁ ተነግሯል።

ይህ ትርዒት ከትዕይንትነት ባለፈ ኢትዮጵያ ለሀገራዊ ብልጽግና እና ለአፍሪካ ትስስር ያላትን ጠንካራ አቋም ያሳየችበት መሆኑ ተገልጿል።

የምሽቱ የድሮን ትርዒት በአፍሪካ ትልቁ የድሮን ትዕይንት መሆኑ ተነግሯል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ‘ኢቴኤክስ 2025’ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል ።

ይህ ኤክስፖ፤ የሳይበር ደህንነት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ፋይን ቴክ፣ ስማርት ሲቲ እና የቴክኖሎጂ ትምህርትን መሰረት ያደረገ አምስት የትኩረት መስኮችን የያዘ ነው።

ከዛሬ ግንቦት 8 እስከ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው ኤክስፖ ከ10 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።