የሀገር ውስጥ ዜና

 ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ግምባር ቀደም ሀገር እየሆነች ትገኛለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

May 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በክሕሎት ማበልጸጊያ ሥራዎች አርአያ እየሆነች መምጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለአፍሪካ ብልጽግና እና ትብብር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካ መድረክ ላይ ተሳተፈዋል፡፡

በመድረኩ ባደረጉት ንግግርም አፍሪካ በሀገር በቀል የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተመራ አካታች ብልጽግና በማምጣት የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት እየሰራች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በክሕሎት ማበልጸጊያ ሥራዎች ግምባር ቀደም ሀገር እየሆነች መምጣቷን ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመሩ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ዲጂታል መታወቂያ እንዲሁም የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና የኢትዮጵያን የዲጂታል ሕልሞች ወደ ተጨባጭ ለውጥ የሚቀየሩ ናቸው ብለዋል፡፡

አፍሪካ በ2030 አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በሥነ ምግባር እና በአካታችነት መርሕ በአህጉራዊ መልክ ልትገነባ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡