የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ዛሬም ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይውላል

By Adimasu Aragawu

May 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ዛሬ ማጠቃለያውን ያገኛል።

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በትናንትናው ዕለት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ መዋሉንና በዛሬው ዕለትም ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚውል የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ከግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ በሚገኘው ኤክስፖው÷ ከ10 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ተሣታፊዎች መገኘታቸውን አመላክተዋል።

ኤክስፖው ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ያሳየችበት ትልቅ መድረክ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያተረፉ ኩባንያዎች መሳተፋቸውንም ጠቁመዋል።

ላለፉት ሁለት ቀናት የሳይበር ደህንነት መሠረተ ልማት፣ ጥበቃ እንዲሁም በዘርፉ ሊቀረፉ ስለሚገባቸው ችግሮች እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የአፍሪካን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ  ለማሳካት ያለውን አስተዋጽኦ የሚያመላክቱ ዉይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተሳታፊ በሆኑ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻዎች መካከል የልምድ ልውውጦች መደረጋቸውንና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ከዓለም አቀፍ፣ ከአህጉራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች አንጻር የሚተነትኑ ጥናታዊ ጽሑፎች በኤክስፖው ላይ ቀርቧል።

በኤክስፖው ከፍተኛ ተቀባይነትና ዕውቅና ያላቸው ከ100 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ማስተዋወቃቸውም ተመላክቷል።

በአድማሱ አራጋው