አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች ከጣልያን ሴሪ ኤ ውጪ አሸናፊዎቻቸውን ለይተዋል።
የጣልያን ሴሪ ኤ የዋንጫውን መዳረሻ ያላገኘ ብቸኛው የአውሮፓ ታላቅ ሊግ ሆኖ እስከመጨረሻው ሳምንት በአጓጊነቱ ቀጥሏል።
የጣልያን ሴሪ ኤ በዚህ የውድድር ዓመት ኢንተር ሚላን እና ናፖሊን ለስኩዴቶ ክብር አፋጦ የመጨረሻው ሳምንት ላይ ደርሷል፤ የአንቶኒዮ ኮንቴው ናፖሊ በ79 ነጥብ ሴሪ ኤውን ሲመራ የሲሞኒ ኢንዛጊ ኢንተር ሚላን በበኩሉ በ78 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በዚህ የውድድር ዓመት ሊጉን ለሳምንታት ሲመራ የቆየው ኢንተር ሚላን በቅርቡ መሪነቱን በናፖሊ ቢነጠቅም እግር በእግር እየተከተለ ይገኛል።በአሰልጣኝ ሲሞኒ ኢንዛጊ የሚመራው ኢንተርሚላን በዚህ የውድድር ዓመት ሁለት ዋንጫ ለማሳካት ብርቱ ፉክክር እያደረገ ነው።
በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ከ11 ቀናት በኋላ ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ጋር የፍጻሜ ፍልሚያ በሙኒክ አሊያንዝ አሬና የሚጠብቀው ኢንተር በሴሪ ኤው ደግሞ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ መሪውን ናፖሊ እየተከተለ ነው።
በሲሞኒ ስር በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒየንስ ሊጉ እያሳየ ባለው ድንቅ ብቃት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አድናቆት የተቸረው ኢንተር ፤ ከግብ ጠባቂው ያን ሶመር እስከ ፊት መስመር ተጫዋቹ ላውታሮ ማርቲኔዝ ያለው ጥምረት ድንቅ መሆኑን በውድድር ዓመቱ ሲያስመለክት ቆይቷል።
ኢንተር ሚላን የስኩዴቶውን ክብር ለመቀዳጀት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታውን ማሸነፍ እና የመሪውን ናፖሊ መሸነፍ አሊያም ነጥብ መጣል መጠበቅ ግድ ይለዋል።የጣልያን ሴሪ ኤ መሪው ናፖሊ አሰልጣኞችን ሲቀያይር ቢቆይም አሁን በኮንቴ ስር ዋንጫውን ለማንሳት ተቃርቧል።
ናፖሊ በ2022/23 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ሉቻኖ ስፓሌቲ እየተመራ ከሶስት አስርት ዓመታት በኃላ ስኩዴቶውን ማሳካት መቻሉ ይታወሳል።
ናፖሊ ከስኩዴቶ ክብር በኋላ ከስፓሌቲ ጋር ተለያይቶ በርካታ አሰልጣኞችን ቢቀጥርም ቡድኑ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ደካማ እንቅስቃሴን ለማሳየት ተገዷል። ጣልያናዊውን አሰልጣኝ ኮንቴ ካገኘ በኋላ ግን በዚህ ወቅት የሴሪ ኤው ሻምፒዮን ለመሆን የአንድ ጨዋታ እድሜ ብቻ ቀርቶታል።
የስኩዴቲውን ክብር ለመጎናጸፍ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ጠብቆ በ2022/23 ያሳካው ናፖሊ፤ ዘንድሮ ዋንጫውን ማሳካት ከቻለ በሶስት የውድድር ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ ባለ ክብር ይሆናል።
ይህን ለማድረግ ደግሞ የራሱን የቤት ስራ በመጨረሻው ሳምንት ከካግሊያሪ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ መወጣት ከቻለ የማንንም ውጤት ሳይጠብቅ ሻምፒዮን መሆን ይችላል።የዋንጫ አሸናፊውን የሚለዩ ሁለት ወሳኝ የጣልያን ሴሪ ኤ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች የቀን ለውጥ እንደተደረገባቸው ይፋ ሆኗል።
የሊጉ መሪ ናፖሊ ከካግሊያሪ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከኮሞ የሚያደርጉት ጨዋታ ከእሑድ ወደ ዓርብ የመጡ ሲሆን ÷ሁለቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ ይደረጋሉ።
ጨዋታዎቹ የቀን ለውጥ የተደረገባቸው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ተፋላሚው ኢንተር ሚላን ተጨማሪ የእረፍት ቀን እንዲያገኝ ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
በአንድ ነጥብ ልዩነት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሴሪ ኤው ሻምፒዮን ለመሆን የተፋጠጡት ናፖሊ እና ኢንተር ሚላን ሊጉን በእኩል ነጥብ ከጨረሱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ለማድረግ ይገደዳሉ።
ናፖሊ ተሸንፎ ኢንተር አቻ የሚወጣ ከሆነ፤ በነጥብ እኩል ስለሚሆኑ የስኩዴቶውን አሸናፊ የሚለየው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያም በሚቀጥለው ሣምንት ሰኞ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ