አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ1 ቢሊየን 325 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሊዝ ፋይናንስ ማሽነሪ አቅርቦት መመቻቸቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አባስ መሐመድ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ተከትሎ በክልሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የንቅናቄው አካል የሆኑ መድረኮች እየተካሄዱ በመሆኑ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እየተለዩ በጋራ የሚፈቱበት ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 14 ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ሥራ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም 62 አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀማቸውን በመለካት ከነበሩበት 48 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በ2016 እና በ2017 በጀት ዓመት በተለያየ የሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ 56 አምራች ኢንዱስትሪዎች 1 ቢሊየን 181 ሚሊየን 300 ሺህ ብር የሥራ ማስኬጃ ብድር ማመቻቸት መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
ከላይ በተገለጸው ጊዜ ለ40 አዳዲስ እና ነባር አምራች ኢንዱስትሪዎች በ1 ቢሊየን 325 ሚሊየን 669 ሺህ 881 ብር የሊዝ ፋይናንስ ማሽነሪ አቅርቦት መመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው