አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለመኸር እርሻ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብዓት ዘርፍ ኃላፊ ግዳልቅ አልቅሚ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ለ2017/18 የምርት ዘመን በቂ የዳፕና ዩሪያ አፈር ማዳበሪያ ግብዓት እንዲኖር ለማስቻል ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህም ለምርት ዘመኑ 330 ሺህ ዳፕ እና 220 ሺህ ዩሪያ በአጠቃላይ 550 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በፌዴራል መንግሥት ግዢ ተፈጽሞ ወደ ክልሉ እየገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እስካሁን 190 ሺህ 797 ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ እና 103 ሺህ 317 ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቀሪውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራ በፌዴራል መንግስት በኩል በቀጣይነት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ግዳልቅ ገልጸዋል።
በክልሉ የአርሶ አደሩን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን አንስተው÷ እስከ ቀበሌ ድረስ የተቀናጁ ሥራዎች እየተከናነ እንደሆነ አመላክተዋል።
በአድማሱ አራጋው