አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን 142 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማር መመረቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የማር ኢኒሺየቲቭ አስተባባሪ ቶሌራ ኩምሳ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ በክልሉ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ባለው የማር ኢኒሺየቲቭ የማር ምርታማነት እያደረገ መጥቷል።
ኢኒሼቲቩ በተጀመረበት ዓመት የተመረተው ማር 60 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት 140 ሜትሪክ ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ እስካሁን ድረስ 142 ሺህ ሜትሪክ ቶን በማምረት ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው ባለፉት ዓመታት በተሰራው ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአየር ንብረት ምቹነት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።
የማር ምርትን በጥራትና በመጠን ለማሳደግ ከባህላዊ የንብ ቀፎ ወደ ዘመናዊ የንብ ቀፎ የማሸጋገር ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም የሚፈለገው ውጤት እየመጣ መሆኑን አመልክተዋል።
ዘንድሮ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ቀፎ ለአርሶ አደሩ መድረሱን ተናግረዋል።
የማር ምርት የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የውጪ ምንዛሬን በማስገኘት እና በስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በአያና ደሬሳ