አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ በ2ኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መከላከል እና የገጠር ልማት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
በብራዚል ዋና ከተማ ብራዚሊያ ዛሬ የተጀመረው ጉባዔው፥ በብራዚልና በአፍሪካ ሀገራት መካከል በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በንግድና በዘላቂ ልማት ዘርፎች ላይ ተጨባጭ እድገት ለማምጣትና ትብብርን ለማጎልበት የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ጉባዔው ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ሰፊ ፋይዳ እንዳለውም ነው የተገለጸው፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከብራዚል ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኢንዱስትሪና ልማት ሚኒስትር ጀራልድ ሮድርጌዝ አልካሚን ጋር ተወያይቷል። አቶ ተመስገን በዚሁ ወቅት፥ የባለብዙ ወገን ትብብርንና ሌሎች ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ አሠራሮችን ለመተግበር በጋራ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያን ፈጣን እድገትና በጥሩ መሰረት ላይ የሚገኘውን የሀገር ውስጥ ምርት መነቃቃትን አድንቀዋል፡፡
ሀገራቸው በተለይም ኢትዮጵያ በምትታወቅበት ጠንካራና ዘመናዊ የአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ የመሥራት ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል፡፡
በፍሬህይወት ሰፊው