አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገሪቱ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
“ንቦችን እንጠብቅ” በሚል መሪ ሐሳብ ዓለም አቀፍ የንብ ቀን እና 2ኛው ዘላቂ የንብ ማነብና እጽዋት ተራክቦ ኮንፈረንስ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ አደም በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም ዋነኛ አቅጣጫ ሆኖ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመው፤ መርሐ ግብሩ ለንብ ማነብና ለማር ምርታማነት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አካባቢያችንን በመንከባከብ የንቦችን ደኅንነት በመጠበቅ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ነው ብለዋል።
የማር ምርትን ለማዘመን በተሰጠው ትኩረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ሀገር 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎ መሠራጨቱንና 250 ሺህ ቶን የማር ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
የንብ አያያዝና ጥበቃ እንዲሁም ምቹ ከባቢን በመፍጠርና አርሶ አደሩን በማብቃት የተሻለ የማር ምርት እንዲገኝ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በአቤኔዘር ታዬ