የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውን አባሰንጋ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው

By Adimasu Aragawu

May 21, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቆላማ አካባቢዎች በዳልጋ ከብቶች ላይ የተከሰተውን አባሰንጋ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ታምሩ ቦኒ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የበሽታው ምልክት በክልሉ በሁለት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ተከስቷል።

በዚህም በሽታው መጀመሪያ ላይ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱርማ ወረዳ መከሰቱን አንስተው÷ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመዛመት እስካሁን 94 የዳልጋ ከብቶች ላይ የሞት አደጋ ማስከተሉን ተናግረዋል።

በበሽታው 120 ከብቶች መጠቃታቸውንና ህክምና ተደርጎላቸው መዳናቸውን ጠቁመው÷ እስከ ትናንት ድረስ ከ173 ሺህ 900 በላይ ከብቶች የመከላከያ ክትባት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

በሽታው እንዳይስፋፋ ለመከላከል አሁንም ክትባት የመስጠት ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ለዚህም ከፌዴራል መንግስት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶዝ የክትባት መድኃኒት እንደተገኘ ገልጸው፤ ከ2 ሚሊየን በላይ የዳልጋ ከብቶችን በአንድ ሣምንት ውስጥ ለመከተብ ወደ ሥራ መገባቱን አመላክተዋል።

በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ክትባቱ የበሽታ ምልክት በታየባቸው ስምንቱም ወረዳዎች እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው÷ ኅብረተሰቡ ከብቶቹን በአግባቡ እንዲያስከትብ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአድማሱ አራጋው