የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 500 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ

By Adimasu Aragawu

May 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አንደኛ ሽናሌ በክልሉ ከ172 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም 375 ሚሊየን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸው፤ ከበልግ ወቅት ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ተከላ እስካሁን 42 ሺህ ሄክታር መሬት በችግኝ መሸፈኑን ጠቁመዋል።

ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ1 ሺህ 201 ችግኝ ጣቢያዎች ለምግብነት የሚውሉትን ጨምሮ የተለያዩ እጽዋት ችግኞች መዘጋጀታቸውንም አቶ አንደኛ ሽናሌ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እስካሁን ለችግኝ መትከያ 202 ሚሊየን ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ጠቀሰው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት ስድስት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ከ419 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን አስታውሰዋል።

ባህል እየሆነ በመጣው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኅብረተሰቡ ዘንድሮም ንቁ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአድማሱ አራጋው