የሀገር ውስጥ ዜና

የባህር በርን በተመለከተ የሚነሳው ጥያቄ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል – ምሁራን

By Yonas Getnet

May 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በር ጉዳይን በተመለከተ የሚነሳው ጥያቄ ሳይቀዘቅዝ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ሲሉ ምሁራን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ጌትዬ ትርፌ መንግስት የባህር በር ጥያቄን አጀንዳ አድርጎ ባቀረበበት ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የመገናኛ ብዙኃን ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው÷ አሁን ላይ ግን እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

አጀንዳውን በተመለከተ የሚነሳው ጥያቄ ሳይቀዘቅዝ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አንስተው÷ የባህር በር ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ የሚዲያ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመንግስት መዋቅሮች እና ሌሎች አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በዚህም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እና የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰው÷ ጥያቄው የቀረበላቸው አካላትም ጉዳዩን ቆም ብለው እንዲያስቡና መልካም ምላሽ ለመስጠት የሚመክሩበትን እድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

ከዓለም ፖለቲካዊ የአሰላለፍ ሁኔታ እና ተለዋዋጭነት አንፃር ኢትዮጵያ የባህር በር የማይኖራት ከሆነ ለኅልውናዋ አስጊ ሊሆን እንደሚችልም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ የሆኑት ጥላሁን ሊበን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የመንግስት ጥያቄ ብቻ በቂ እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን መሰለፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የፐብሊክ እና ዲጂታል ዲፕሎማሲን ጨምሮ ሌሎች የዲፕሎማሲ መንገዶችን በመጠቀም ከተረባረበ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማሳካት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

ቀይ ባህር የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ስበት እንደሆነና በቀጣናው የባህር በር ያላቸው ሀገራት ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ያሉት ተመራማሪው÷ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆንና ሉዓላዊነትን ለማስከበር የባህር በር ባለቤትነት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የባህር በር ጉዳይ ከፀጥታ እና ከሀገር ሚስጥር መጠበቅ አንፃር እጅግ ወሳኝ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በአትኩሮት ሊሰራበት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዮናስ ጌትነት