የሀገር ውስጥ ዜና

የቀይ ባሕር አካባቢን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው ሀገራት ትብብር ወሳኝ ነው

By Adimasu Aragawu

May 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው ሀገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ተናገሩ።

3ኛው የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲካ ፎረም “የቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ቀጣና ሀገራት ለኢኮኖሚያዊ፣ ለደኅንነት ትብብር እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው ሀገራት ትብብር ወሳኝ ሚና አለው።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የጋራ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗን እንደገለጹ የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ የባህር ላይ ዝርፊያዎችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚኖራት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።