አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ሳን ዲዬጎ የመኖሪያ መንደር በጭጋጋማ የአየር ንብረት ምክንያት አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሷል።
የተከሰከሰው አውሮፕላን 15 ቤቶች እና በርካታ መኪናዎች በእሳት እንዲያያዙ ማድረጉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
አውሮፕላኑ በአካባቢው በሚገኙ ቤቶች ላይ በቀጥታ መውደቁን የገለጹት ባለስልጣናት÷ የአውሮፕላን ነዳጅ መፍሰሱንና አደጋው በተከሰተበት አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መታዘዙን አመልክተዋል።
በአካባቢው የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች አውሮፕላኑ ባደረሰው አደጋ ምክንያት መዘጋታቸው ተገልጿል።
የተከሰከሰው አውሮፕላን ከስድስት እስከ ስምንት ሰዎችን ማጓጓዝ የሚችል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን÷ ምን ያህል ሰዎች በአውሮፕላኑ ውስጥ እንደነበሩ እና የደረሰ ጉዳት እስካሁን ይፋ አለመሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዮናስ ጌትነት