የሀገር ውስጥ ዜና

የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ 90 በመቶ ደረሰ

By Hailemaryam Tegegn

May 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሂደት 90 በመቶ መድረሱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አመለወርቅ ሕዝቅኤል ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ሂደት ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሂደት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን መግለጻቸውን አመልክተዋል።

የግንባታ ሂደቱን ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ አውሮፕላን ማረፊያውን ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ እንደሆነም ተመላክቷል።

ያቤሎ እና አካባቢው ከፍተኛ የቀንድ ከብት እርባታ የሚካሄድበትና ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት ያለበት ስፍራ በመሆኑ አውሮፕላን መረፊያው ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።

ከዚህም ባለፈ በአካባቢው ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ግንባታው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው በየደረጃው ያለው አመራር እና የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።

ከያቤሎ በተጨማሪ በነገሌ ቦረና፣ መቱ ጎሬ፣ ሚዛን አማን እና ደብረማርቆስ በተመሳሳይ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።

በፀሀይ ጉልማ