አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ብራዚል በግብርናው ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸውን በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ያጋራችበት ሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መከላከል እና የገጠር ልማት ጉባዔ በብራዚል ተካሂዷል፡፡
ጉባዔውን በተመለከተ አምባሳደሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እና ብራዚል በግብርናው ዘርፍ በጋራ ለመስራት እና ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ስምምነቱ በግብርናው ዘርፍ ለምንሰራቸውን ስራዎች ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ያሉት አምባሳደሩ፤ ብራዚል በሠራችው ስኬታማ ሥራ በግብርናው ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዕለ ሃያል መሆን መቻሏን አንስተዋል፡፡
ጉባዔው ብራዚል እና አፍሪካ ልምድ በመለዋወጥ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በጋራ መስራት እንደሚችሉ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌማት ትሩፋት እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎችን ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት እንድናካፍል ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ