አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 9 ወራት 107 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዲስ ደንበኞች መስተንግዶ፣ ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭና ከሌሎች ልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ለመሰብሰብ ከታቀደው የገንዘብ መጠን 97 በመቶ አፈፃጸም መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር÷ባለፉት ዘጠኝ ወራት 356 ሺህ 935 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማጠናከር እየተደረገ ባለው ጥረት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት በኢ-ፔይመንት የተሰበሰበው 93 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል 107 የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በማድረግ የተቀመጠውን እቅድ መቶ በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው ለፋና ዲጂታል የተናገሩት፡፡