የሀገር ውስጥ ዜና

በግብርናው ዘርፍ ምርምር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለብን ተሞክሮ ወስደናል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

By ዮሐንስ ደርበው

May 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በግብርናው ዘርፍ ጥናት እና ምርምር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለብን ከብራዚል ተሞክሮ ወስደናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡በሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መከላከል እና የገጠር ልማት ጉባዔ ተሳትፎ ዙሪያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡በማብራሪያቸውም፤ በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በእነዚህ ዘርፎች ያላትን ተሞክሮ ለአፍሪካ ሀገራት እና ለብራዚል ማሳየት መቻሏን ተናግረዋል፡፡የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስርት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በተለያዩ ጉዳዮች አብሮ ለመስራት መነጋገራቸውን አስታውሰው፤ ከዚያ በኋላ በርካታ ስራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ብራዚል በግብርና ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ትልቅ ለውጥ ማምጣቷን በጉብገኝታችን ወቅት ተመልክተናል ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡ለብራዚል የግብርና ዘርፍ ዕድገት የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸው ተገንዝበናል ያሉት አቶ ተመስገን፤ እኛም በግብርናው ዘርፍ ጥናት እና ምርምር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለብን ተሞክሮ ወስደናል ብለዋል፡፡በወንድማገኝ ጸጋዬ