አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሊቨርፑል የፊት መስመር ተጨዋች ሞሐመድ ሳላህ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 የውድድር ዘመን የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡
ግብፃዊው ኮከብ ሳላህ በዚህ የውድድር ዓመት ለሊቨርፑል ባደረጋቸው 37 የሊጉ ጨዋታዎች፤ 28 ግቦችን አስቆጥሮ 18 ወደ ግብነት የተቀየሩ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡
በ28 ግቦችም የሊጉን ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል፡፡
ሳላህ በሊጉ ታሪክ ሁለት ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ሽልማት በማሸነፍ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ቴሪ ኦንሪ፣ ኒማንያ ቪዲች እና ኬቨን ዴብሮይን ጋር ክብረ ወሰን ተጋርቷል፡፡
በዚህ የውድድር ዘመን ከሊቨርፑል ጋር የሊጉን ዋንጫ ማሳካት የቻለው ሞሐመድ ሳላህ ለሊቨርፑል ዋንጫ ማሳካት ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 የውድድር ዓመት በነገው ዕለት ፍፃሜውን ያገኛል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ