የሀገር ውስጥ ዜና

በሀረሪ ክልል 35 ህገወጥ ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

By Meseret Demissu

August 09, 2020

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 3 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል 35 ህገወጥ ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው÷ በክልሉ ሶፊ ወረዳ የፀጥታ ሀይሉ ባደረገው ቅንጅታዊ ስራ 35 ሽጉጦችና 2 ክላሾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልፀዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹን ይዘው የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ  ዋና ኢንስፔክተር ያህያ አብዱሰላም አስታውቀዋል።

ሀላፊው አያይዘውም በክልሉ በተለያዩ ግዚያት ሲነሱ የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲባል በተያዘለት እቅድ መሰረት የመከላከያ ሰራዊት ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የፌደራልና የሀረሪ ፖሊስ በጋራ በመቀናጀት በሶፊ ወረዳ ባደረጉት የኦፕሬሽን ስራ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹና 1 ኮምፒዩተር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ከዚያም ባለፈ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ሲያውኩና ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ወንጀል ፈፅመው ለህግ ያልቀረቡ ፣ሁከትና ብጥብጥን ሲመሩና ሲሳተፉ የነበሩ ሀምሳ ተጠርጣሪዎች ህብረተሰቡ በሰጠው መረጃ መሰረት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በምርመራ እየተጣራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።

የፀጥታ ሀይሉ በፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራርም በወረዳው ብሎም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ህብረተሰቡ የጎላ ሚና ስላለው በአካባቢው ስላለው የፀጥታ ችግር ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመቆም ተገቢውን መረጃና ድጋፍ እንዲሰጥ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ህዝባዊ መድረኮች መፈጠራቸውን ኮማንደር ጣሰው ገልጸዋል።

በተሾመ ኃይሉ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።