የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በመኸር እርሻ 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል ይሸፈናል

By Yonas Getnet

May 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በ2017/18 የመኸር እርሻ 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል እንደሚሸፈን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ በመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

በምርት ዘመኑ የመኸር ወቅት 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸው፤ እስከ አሁን 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱን ተናግረዋል።

ባለፈው የምርት ዘመን ወደ 170 ሚልየን ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውሰው፤ የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በተያዘው ምርት ዘመን 187 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

በቆሎ እና ማሽላ መዝራት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በአብዛኛው አካባቢ የማሣ ዝግጅት እና እርሻን የማለስለስ ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመኸር ወቅት ለማረስ ከታቀደው መሬት ውስጥ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ለማረስ ታቅዶ የመሬት ልየታ እና አርሶ አደሮችን የማደራጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሜካናይዜሽን ዘዴ 981 ሺህ ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ የሰብል ልማት ፓኬጅ ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።

በዮናስ ጌትነት