የሀገር ውስጥ ዜና

የፈፃሚዎችና የነጋዴዎች ጉድለቶችን በትብብር ለማረም ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተግባብተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Yonas Getnet

May 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንዳንድ ፈፃሚዎች እና ነጋዴዎች ዘንድ የሚታዩ የስነ ምግባር ጉድለቶችን በትብብር ለማረም ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ከተለያዩ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ከተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ምክትል ኃላፊ አቶ በረከት ታከለ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ተመሳሳይ መድረክ ከዚህ ቀደም ለሶስት ጊዜ የተካሄደ ሲሆን የዛሬው አራተኛ እና ማጠቃለያ መሆኑን ገልጸው፤ በየደረጃው ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረገው ውይይት መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

በመድረኩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማችንን እንደ ስሟ ውብ እና አዲስ እያደረጉ ያሉ በርካታ የልማት ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለነዋሪዎቻችን ግልጋሎት ክፍት እንድናደርግ ያገዙንን ግብር ከፋዮቻችንን አመስግነናል ብለዋል።

በተጨማሪም ህፃናት ተመግበዉ፣ ተመሳሳይ ዩኒፎርም ለብሰው እና የትምህርት ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው እንዲማሩ በማስቻል ረገድ ግብር ከፋዮቹ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች በፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እና ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ዝርጋታ፣ የአሰራር ስርዓት በማዘመን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በአንዳንድ ፈፃሚዎች እና ነጋዴዎች ዘንድ የሚታዩ የስነ ምግባር ጉድለቶችን በማረም እንዲሁም የፈፃሚዎችን አቅም በማሳደግ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጥ ለማሳደግ በትብብር ለመስራት መግባባት የተደረሰበት መሆኑን አቶ በረከት አንስተዋል።

በዮናስ ጌትነት