የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

By Yonas Getnet

May 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 628 ሺህ 463 ሕጻናትን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ መሰጠት ጀመረ፡፡

ለ10 ቀናት በሚቆየው በዚህ ዘመቻ ዕድሜያቸው ከ9 ወር እስከ 5 ዓመት ለሆኑ ሕጻናት እንደሚሰጥ እና ለዚህም 314 የክትባት ቡድኖች ተዋቅረው ሥራ መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ዘመቻው በ96 ጤና ጣቢያዎች እና 1 ሺህ 536 ጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሕጻናቱ ከዚህ በፊት በመደበኛም ሆነ በዘመቻ ቢከተቡም ባይከተቡም አሁን መሰጠት የጀመረውን ማጠናከሪያ ክትባት መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከዘመቻው ጎን ለጎን መደበኛ ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናት ክትባት እንደሚሰጥም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ለነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች የሥርዓተ-ምግብ ልየታ፣ የቫይታሚን ‘ኤ’ ጠብታ፣ የአንጀት ትላትል ክኒን፣ የታመሙ ሕጻናትን መለየትና ወደ ጤና ተቋም የመላክ እና በወሊድ ምክንያት የፌስቱላ ችግር ያጋጠማቸው ሴቶችን በመለየት ወደ ሕክምና የመላክ ሥራ ከዘመቻው ጎን ለጎን እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በሲፈን መኮንን