ቢዝነስ

ፋብሪካው ከ38 ሺህ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል አጥቦ ሸጠ

By ዮሐንስ ደርበው

May 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢቲ ማዕድን ልማት አ.ማ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ እና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 38 ሺህ 91 ቶን የድንጋይ ከሰል አጥቦ መሸጡ ተገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የተገነባውን ኢቲ ማዕድን ልማት አ.ማ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ እና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡

በዚሁ ወቅትም፤ ፋብሪካው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የድንጋይ ከሰል ምርት ከማሻሻል ባሻገር ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር መናገራቸው ይታወቃል፡፡

የፋብሪካውን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገ/ማርያም ሰጠኝ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ፋብሪካው በቀን 3 ሺህ 600 ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም አለው፡፡

ከተመረቀበት ጊዜ ጀምሮም በቀረበለት ግብዓት ልክ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 38 ሺህ 91 ነጥብ 55 ቶን ከሰል ታጥቦ መሸጡን አንስተዋል፡፡

ከዳውሮ ዞን አራት አምራቾች ለፋብሪካው ጥሬ ከሰል እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከኮንታ ዞን አምራቾች እንዲያቀርቡ ተፈቅዶ ሌሎች በሂደት ላይ ሲሆኑ አንዱ አምራች ማቅረብ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡

ፋብሪካው ለሀገሪቱ ከሚያስፈልገው የድንጋይ ከሰል 25 በመቶ ማምረት የሚችል ሆኖ ሳለ፤ የጥሬ ከሰል አቅርቦቱ ውስን በመሆኑ በሙሉ አቅሙ እየሠራ አይደለም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ፋብሪካው ለ195 ወገኖች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው