አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አዲስ አበባን ውብ እና ጽዱ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከተማ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በተለይም በኮሪደር ልማት የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የኮንፈረንስ መዳረሻነቷ ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የዘመናዊ ከተማነት ደረጃን ያሟላች እንድትሆንና የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው÷ የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን ዕድገት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በአርአያነት የሚጠቀስ እንደሆነ አውስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎችን ተዘዋውረው እንደጎበኙ የገለጹት ሊቀመንበሩ÷ በዚህም በከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ለውጥ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
በመዲናዋ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ጭምር የሚስተዋለው የነዋሪዎች የሥራ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በአዲስ አበባ የተከናወነው የልማት ሥራ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማት ከተማነቷን የሚመጥን መሆኑን ገልጸው÷የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አዲስ አበባ ከሌሎች አፍሪካ ከተሞች ጋር ያላት ሁሉን አቀፍ ትስስርና ትብብር ይበልጥ እንዲስፋፋ በትብብር እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት ለፋና ዲጂታል አስታውቋል፡፡
በመላኩ ገድፍ