የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ጎንደር ዞን በትራፊክ አደጋ የ7 ሰዎች ሕይወት አለፈ

By Melaku Gedif

May 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ጎንደር ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሰባት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡

አደጋው 18 ሰዎችን አሳፍሮ ከጎንደር ወደ ባሕር ዳር ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ይፋግ ንዑስ ጣቢያ አካባቢ ከቆመ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ መከሰቱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ሥራ ሒደት ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ሽባባው አለባቸው ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ በአደጋው የሰባት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን÷ ሌሎች ተሳፋሪዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል።

ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በአዲስ ዘመን ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንና የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

በሹመት አለማየሁ