አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤም ፖክስ (Mpox) በሽታ እንዳይዛመት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፡፡
ሚኒስትሯ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ አስተዳደር በኤም ፖክስ ከተጠረጠሩ ሰዎች በተወሰደ ናሙና እስካሁን የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች ላይ በሽታው ተገኝቷል፡፡
በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ÷ ሕብረተሰቡ መረጃዎችን በአግባቡ በመከታተል ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው ለመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ኤም ፖክስ ከተያዘ ሰው ጋር በአካል ንክኪ ወይም በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን÷ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡
ሽፍታ፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የእጢ እብጠት፣ የቆዳ ቁስለትና ድካም እንዲሁም የጡንቻ እና የጀርባ ሕመም የበሽታው ምልክቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ተጋላጭነት ይታይባቸዋል የተባሉ ቦታዎችን በመለየት በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በድንበር አከባቢ እና በሁሉም መውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን ዶ/ር መቅደስ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው÷ በሽታው መከሰቱ ከተረጋገጠ ጊዜ ጀምሮ ግብረ ሃይል በማቋቋም በትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዜጎች ከላይ የተጠቀሱት የበሽታው ምልክቶች ሲስተዋሉባቸው አቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በ8335 አጭር የጽሑፍ መልዕክትና በ952 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ