የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 439 ሺህ ኩነቶች ተመዘገቡ

By ዮሐንስ ደርበው

June 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት 439 ሺህ ኩነቶችን መዝግቤአለሁ አለ የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት።

የአገልግሎቱ ዳይሬክተር መዓዛ በዛብህ እንዳሉት፤ ከ439 ሺህ ኩነቶች መካከል ከ40 ሺህ የሚልቁት በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ማደራጀት ተችሏል፡፡

በዚህም ለክብር መዝገብ ሕትመት ሊወጣ የነበረን 2 ሚሊየን ብር ወጪ ማዳን መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

መረጃው ለሕጻናት አስተዳደግ፣ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ለቀልጣፋ አገልግሎት፣ ለአስተዳደርና ውሳኔ ሰጪ አካላት ወሳኝ ስለሆነ ሁሉንም መዝገቦች በአንድ ቋት ለማስቀመጥ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ይህንን ለማሳካት የ5 ዓመት የቴክኖሎጅ ዕቅድ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን አውስተው፤ በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻ እና ደሴ ከተሞች 122 የምዝገባ ጣቢያዎች ተግባራዊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ተቋማቸው ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያለማውን ሲስተም ዛሬ በደብረብርሃን ከተማ ያስተዋወቀ ሲሆን፤ በቀጣይ 5 ዓመታት በክልሉ ባሉ 4 ሺህ 17 የምዝገባ ጣቢያዎች ተግባራዊ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

በሳምራዊት የስጋት