የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያዊነት ጥቅም ስናገኝበት የምናዜመው፤ ሲከፋን የምንተወው የወረት ጉዳይ አይደለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

June 04, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊነት ሲመቸን፣ ሲደላን፣ ጥቅም ስናገኝበት የምናዜመው የምናወድሰው ሲከፋን ሳይመቸን ሲቀር ህልሞቻችን ሲጨነጋገፉ የምንተወው የወረት ጉዳይ አይደለም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች አስመልክቶ ባደረጉት ልዩ ባለ አራት ክፍል ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል፤ የኢትዮጵያዊነት ምንነት ላይ ሳንግባባ ከዚያ በኋላ የሚመጡ ሐሳቦች ላይ መነጋገር ያስቸግራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማን ነው፤ ኢትዮጵያዊስ ማን ነው፤ ለምንድን ነው ኢትዮጵያዊነትን የሁላችን አሰባሳቢ ጥላ አድርገን የምንወስደው የሚለውን ነገር ሁሉም ሰው በእኩል ትርጉም ይገነዘበው እንደሆነ እርግጠኛ እንዳልሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ለእኔ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕጣ ፋንታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ሕዝብ የምንደርስበትን ማንኛውም ትልሞቻችንን ልናሳካ የምንችለው በዚህ መሠረታዊ የጋራ አሰባሳቢ አስተሳሰብ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሲባል የግለሰብ ጥቅም፣ የማኅበረሰብ ጥቅም ከዚህ አልፎ ብሔራዊ ጥቅም ማለት ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ብሔራዊ ጥቅም ልክ እንደ ግለሰብ ጥቅም ጠዋት ከፍለን ወዲያው የምናገኘው ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን እኛ ከፍለን ለልጆቻችን ሊሆን ይችላል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

እኛ ሲፈጥረን ባለብዙ መልክ፣ ባለብዙ ቋንቋ፣ ባለብዙ ባህል ስለሆንን እነዚያ የሚለያዩን ማንነቶች ዋናውን ማንነት እንዳይሸረሽሩት የሚያሰባስበን እንደ ቤተሰብ እንድንታይ የሚያደርገን ትርክት ያስፈልገናል ነው ያሉት፡፡

ከዚያም ባሻገር ብሔራዊ ጥቅም ያልነውን ነገር ሊያሳካ እና ሊያበለጽግ የሚችል ትውልድ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ጥቅም ማለት ከግል ጥቅም የተሻገረ እና በትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያዊነትን ማጽናት ማለት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በእርግጥ ከግምት መግባት ያለበት እና እንደችግር የሚታይ የማንነት አረዳድ ችግር አለ፤ አንድ ሰው በአንድ ማንነት መታወቅ እንደማይችል መታወቅ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ትልቁ ማንነት ግን ሰብሳቢው ኢትዮጵያዊነት ነው ብለዋል፡፡

ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ የሚለው ሐሳብ ገዥ ነው፡፡ በውስጡ ጥልቅ ሐሳብ ይዟል፡፡ ስንሞት እንኳን የምናርፍበትን ሀገር ማቆት ግድ ይላል፡፡ ሀገር የቅብብሎሽ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ለመጭው ትውልድ እንዴት አድርገን የጸና፤ የለማ የማይለምን ሀገር እናቆያለን ከሚል ፍሬ ሐሳብ ጋር መሰናሰል ግን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

አባቶቻችን ያቆዩትን ቅርስ እንዲቆይ የምንጠግነው፤ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሻገሩ በማሰብ ነው፤ ትውልድን ያሰብን፤ ነገን እያሰብን ነው እሠራን ያለነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ መጠይቃቸው፡፡

ትናንትን በወጉ መገንዘብ፤ የጎደለውን እየሞሉ ለቀጣዩ ማሻገር ነው ኢትዮጵያዊነት፤ ኢትዮጵያዊነት ሲመቸን፣ ሲደላን፣ ጥቅም ስናገኝበት የምናዜመው የምናወድሰው ሲከፋን ሳይመቸን ሲቀር ህልሞቻችን ሲጨነጋገፉ የምንተወው የወረት ጉዳይ አይደለም ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት ኩልል ብሎ የሚፈስ ጅረት ነው፤ ክረምት ከበጋ የማይቋረጥ በድምጸቱ፣ ለተጠሙ በመድረሱ፣ ለእርሻ በመዋሉ እርካታን የሚሰጥ ጅረት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜም ዘንቦ ሊደፈርስ ይችላል፤ ነገር ግን ሰክኖ ይጠራል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የማይቆም በቀጣይነት የሚፈስ በሙላት የሚመለስ በልጆች የሚገለለፅ የኖረ፤ ያለ እና የሚኖር ነው ኢትዮጵያዊነት ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው