አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መንግስት የከተሞች ውበት እና የተጥሮ ሀብት ተጠብቆ እንዲዘምኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል አሉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ባህርዳርን ወደ ምቹ ከተማነት ለማሸጋገር የሚረዱ የመንገድ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት እና የተቋማት ዕድሳት ስራዎች በከፍተኛ ርብርብ እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውንም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
ከተማይቱን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪስቶች ተወዳጅ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ደግሞ ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ይበሉ የሚያሰኙ ናቸውም ነው ያሉት፡፡
የተጀመሩ መልካም ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተጨማሪም ፕሮጀክቶችን በጥራት ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግስት የከተሞች ውበት እና የተጥሮ ሀብት ተጠብቆ እንዲዘምኑና የቱሪስት መስህብነታቸው እንዲጨምር ክትትል እና ድጋፍ ለሚሹ ጉዳዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ሲሉም አክለዋል፡፡