የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ያስቻለ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቷል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

June 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቷል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ።

ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 34ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም ፥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የጎረቤት ሀገራትን የሚያስቀድም ስትራቴጂ እና መርሕ የሚከተል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሰረተ ልማት ትስስር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ በጋራ ሰላምና ደኅንነት ዲፕሎማሲ ስኬታማ የትብብር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ባለፉት 9 ወራት ብቻ በአፍሪካ ሀገራትና በመካከለኛው ምስራቅ በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ከ92 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅም ከቀጣናዊ ኃይሎችና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ለቀጣናው ኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር ወሳኝ ሚና የምትጫወት ሀገር ስለመሆኗ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች እየተረጋገጠ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡

የባሕር በር ጥያቄን ለማሳካት የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እውን እስኪሆን ድረስ በዓለም አቀፍ ሕጎች እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።