አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በእውቀትና በጥበብ ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ መሆኑ በሌሎች ሀገራት ጭምር ተመስክሮለታል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት፣ ወቅታዊ ፈተናዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች አስመልክቶ ባደረጉት ሁለተኛው ክፍል ልዩ ቃለ መጠይቅ፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ትግበራ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስፈለገው በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ወይም በዓለም ባንክ ጫና ሳይሆን በሀገሪቱ ያሉ ሁኔታዎች ኢኮኖሚው ክፍት እንዲደረግ በማስገደዳቸው እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ኢኮኖሚውን መክፈት አስፈላጊ መሆኑ ከታመነበት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ወዳደረጉ ሀገራት ልዑካን በመላክ ጭምር ልምድ ለመቅሰም ሰፊ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ማሻሻውን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ከዓለም ባንክና ከልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ማህበራትና ተቋማት ጋር ጥልቅ ውይይቶች መደረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም በውይይቶቹ የተገኙ ልምዶችንና የኢትዮጵያን ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ በማገናዘብ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ 1 እና 2 አማካኝነት ኢኮኖሚው መከፈቱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ደመወዝ የመክፈልና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በመጀመሪያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ 10 ቢሊየን ዶላር በማሰባሰብ ስኬታማ ትግበራ ማድረግ መቻሉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ነገር ግን ወደ ሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን ለመተግበር የሚያስችል ሀብት ለማግኘት ከመጀመሪያው የተለየ መንገድ መከተል አስፈላጊ ነበር ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀጥታ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ወይም ከሌላ ቦታ መጥቶ የተጫነ የሌሎች ፍላጎት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
አይ ኤም ኤፍ ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ያለው እውቀት ውስን በመሆኑ ከተቋሙ ተቀድቶ የመጣ ሪፎርም ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ የተገኘውን ውጤት ሊያስገኝ እንደማይችል ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም ተቋሙ የኢትዮጵያ የሪፎርም ሀሳብ ከቀረበለት በኋላ በ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሊተገበር ይችላል የሚል መከራከሪያ አቅርቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም በኢትዮጵያ በርካታ ሰራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ መሆናቸውን በመጥቀስ የደመወዝ ጭማሪ ካልተደረገ ሪፎርሙ አደጋ ይገጥመዋል የሚል አቋማችንን በግልጽ አሳውቀናል ብለዋል፡፡
መንግስት በገፍ ሲበደር ቆይቶ መመለስ የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የመንግስትና የባንክ ግንኙነት በህግ መመራት ሲጀምር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይወድቃል የሚሉ ስጋቶች መቅረባቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እንዲሆን በመስማማት ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
ሆኖም ካሉት በርካታ ችግሮች አንጻር 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በቂ አለመሆኑን ገልጸው፥ ባለፈው አመት ብቻ መንግስት ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለሴፍቲኔት፣ ለመድሃኒት 350 ቢሊየን ብር ድጎማ አድርጓል ብለዋል፡፡
ድጎማውን ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ያላት አቅም ከግምት እንዲገባ በማስረዳት ከአይ ኤም ኤፍ እና ከዓለም ባንክ ከእያንዳንዳቸው 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች የእዳ ሽግሽግ በማድረግ ሪፎርሙ መተግበሩን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ብቻ የተተገበረ ሪፎርም አለመሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያን ፍላጎት መሰረት በማድረግ፣ የሌሎች ሀገራትን ልምድ በመውሰድና በማማከር በእውቀት፣ በጥበብና በጥልቀት በመወያየት ተግባራዊ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት በቅርቡ በአይ ኤም ኤፍ እና በዓለም ባንክ አመታዊ ስብሰባ ላይ በሁለቱም ተቋማት እንዲሁም በሌሎች ሀገራት በአንድ ድምጽ እንደተመሰከረለት ተናግረዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ