የሀገር ውስጥ ዜና

የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻነት እንዲጨምር አድርጓል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

June 07, 2025

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻነት እንዲጨምር አድርጓል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ባለ አራት ክፍል ቃለ ምልልስ በመጨረሻ ክፍል የኮሪደር ልማትን እንደመንግስት አቅዶ መስራት ያስፈለገበት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የጤና፣ የሕዝብ ቁጥር፣ የከተሜነት መስፋፋት እና ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡

ከተማ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እና ለጤና የሚመች ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ለሁሉም በተመቸ መንገድ ከተማን መስራት አሁን ካልጀመርነው የባሰ አደጋ ከፊታችን ይደቀናል ብለዋል።

በውጭ ሀገራት የተመለከትኳቸው የማይቻል የሚመስሉ ሥራዎች አሁን ላይ እንደሚቻል ምልክቶችን አይቻለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ውበትን ማድነቅ የማይችል ሰው ተፈጥሮን ማድነቅ አይችልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ተፈጥሮን ማድነቅ የማይችል ሰው ደግሞ መፍጠር አይችልም፤ውበትን ከተፈጥሮ ሳንለይ ማድነቅ፣ መፍጠርና ማስዋብ ያስፈልጋልነው ያሉት፡፡

በከተማዋ ለሥራና ለሌሎች እንቅስቃሴዎች እንቅፋት ሆኖ ጊዜ እና ገንዘብ እንዲባክን ሲያደርግ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ በተሰራው የኮሪደር ልማት ሥራ መቀነስ እንደተቻለ ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ማለት የመንገድ መብራት፣ የስልክ እና የኤሌክትሪክ መስመር፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች የሚቀበሩበት እንዲሁም የውጪ ሀገራትን ለማየት እድል ያገኘ ሰው የቀናበት እና የተቆጨበትን ነገር በሀገሩ ማየት ማለት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ትልቅ ሃብት የሚንቀሳቀስበት ለሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተው÷ በዚህ ዓመት ብቻ እስከ 70 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች እንዲካሄዱ ማድረጉን፤ ይህም እያደገ ወደ መላው ኢትዮጵያ እንደሚስፋፋ አመልክተዋል።

አዲስ አበባን መቀየር የሚችል ሥራ ከሰራን ሌሎች ከተሞች ይቀየራሉ፤ ይህ የኢትዮጵያ ልምድ ደግሞ ለመላው አፍሪካ የሚተርፍ ይሆናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኮሪደር ልማት በጣም ጠቃሚ፣ ውጤት ያየንበት፣ ዓለም የሚመሰክርለት እና የሚታይ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይሄንን ሥራ ግራ ቀኝ ሳንል በመተባበር ኢትዮጵያን ማስዋብ አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

በዮናስ ጌትነት