አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ አሥተዳደር ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በሚልቅ ወጪ በአራት ወረዳዎች እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በያዝነው የበጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
የድሬዳዋ አሥተዳደር የፕሮጀክት ግንባታ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወንደሰን ጀንበሬ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በወረዳ 1፣ 2፣ 3 እና 4 የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
27 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሥራ ለማከናወን መታቃዱን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ዙር እየለማ ያለው 11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እየለማ ከሚገኘው መካከልም 5 ነጥብ 75 ኪሎ ሜትሩ 97 በመቶ መድረሱን እና 3 በመቶው በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል፡፡
ቀሪውን 5 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ደግሞ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የመኪና መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የሳይክል መንገድ፣ የጎርፍ ማፋሰሻ መስመር፣ የመንገድ ዳር የጥላ ዛፍና መቀመጫዎች፣ ሱቆች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፣ የሕጻናት መዝናኛ፣ የሕዝብ መዝናኛ፣ ፋውንቴን፣ የመንገድ ዳር ስማርት መብራቶች፣ የመንግሥት ተቋማትን አጥር ማስተካከል፣ የተቀናጀ የመሠረተ-ልማት መስመሮች ዝርጋታና ካፍቴሪያዎችን ያካትታል ብለዋል፡፡
አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚጠይቅ እና ይህም 82 ነጥብ 19 በመቶ በአሥተዳደሩ፣ 11 ነጥብ 2 በመቶ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እና 6 ነጥብ 89 በመቶ በድሬዳዋ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ እንደሚሸፈን ነው ያስረዱት፡፡
በሌላ በኩል ኮሪደሩ በሚያልፍበት መንገድ ዳር ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት ንብረታቸውን በራሳቸው ኃይል በማንሳትና አጥራቸውን ዲዛይኑ በሚፈቅደው መሠረት ማስተካከላቸውን ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው